የዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ከጋሞ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር ከጋሞ ዞን እና በዞኑ ከሚገኙ 14 ወረዳዎችና 4 ከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ 37 የቋንቋ ጥናት ባለሙያዎች እንዲሁም ለወረዳና ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ከሚያዝያ 4 - 7/2013 ዓ/ም በቋንቋ ጥናት ዘዴዎች፣ በመረጃ አሰባሰብ ሂደት፣ በስነ-ቃል እና በስነ-ጽሑፍ ጥናት ላይ ያተኮረ የክሂሎት ማሻሻያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ር መሐመድ ሹሬ እንደገለጹት የሥልጠናው ዓላማ በባለሙያዎቹ ዘንድ ያለውን የክሂሎት ክፍተት በመቅረፍ በዘርፉ ለሚከናወኑ ተግባራት የበቁ እንዲሆኑ ማስቻልና የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት የአካባቢውን ባህል እንዲያሳድጉ ማድረግ ነው፡፡

የአማርኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ት/ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ኃይላይ ተስፋይ የቋንቋ ጥናት አካሄድን አስመልክቶ በሰጡት ሥልጠና ምርምር ከተለምዷዊ ሂደት ወጥቶ ወደ ሳይንሳዊ ሂደት እንዴት መግባት እንዳለበት፣ መነሻ ምክንያቶችን ማዋቀርና ጥያቄዎችን መቅረጽ እንዲሁም የመረጃ አሰባሰብና አገላለጽን አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እያንዳንዱ ባለሙያ ምርምር ሲሠራ መረጃዎችን እንዴት አጉልቶና አካቶ ማቅረብ እንዳለበትና ተግባራዊ ከማድረግም አንፃር የምርምሩ ዓላማ ወሳኝነት እንዳለው ዶ/ር ኃይላይ አስረድተዋል፡፡

የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህር ዶ/ር እንዳልካቸው ኃይሉ የስነ-ጽሑፍና የስነ-ቃል ምንነትና ጥናት ላይ በሰጡት ሥልጠና እንዳብራሩት ስነ-ጽሑፍና ስነ-ቃልን ማጥናት የቋንቋ ችሎታችንንና አጠቃላይ ስብዕናችንን ከማዳበሩም ባሻገር ስነ-ቃሉና ስነ-ጽሑፉ የወጣበትን ማኅበረሰብ የበለጠ ለማወቅ ይረዳል፡፡ የፈጠራ ችሎታችንን ከማሳደግ በዘለለ ምክንያታዊ በመሆን የተለያዩ ባህሎችና አስተሳሰቦችን የሚያስተናግድ ሰፊ ስብዕና እንዲኖረን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ዶ/ር እንዳልካቸው ተናግረዋል፡፡ ስነ-ቃልን ከመሰብሰብ ጀምሮ በመጽሐፍ መልክ እንዴት መሰነድ ይቻላል የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችንም በሥልጠናው ዳስሰዋል፡፡

የጋሞ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የቋንቋና ስነ-ጥበብ ጥናትና ልማት ዋና ሥራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ሸዋ ኃይሌ እንደገለጹት መሥሪያ ቤቱ በባለሙያዎቹ ዘንድ የነበረውን ክፍተት በመለየት ዩኒቨርሲቲውን በጠየቀው መሠረት ሥልጠናውን በመስጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም የተለያዩ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀትና ክትትል በማድረግ ረገድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬቱ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ባህልና እሴቶች እንዳይረሱ እንዴት መሥራት እንዳለባቸው አቅጣጫ ያመላከተ እንደሆነ ገልጸው በቀጣይ የማኅበረሰቡን አመለካከትና ባህሉን በማጥናት እየተረሱ ያሉ ባህሎችን አጉልተው በማውጣት ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ለማሳደግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት