የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ከግብርና፣ ከሕክምናና ጤና እንዲሁም ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጆች ጋር በመተባበር 7ኛውን ‹‹ሳይንስ ለዘላቂ ልማት›› ሀገር አቀፍ የምርምር ዓውደ ጥናት ከሚያዝያ 8-9/2013 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሰቲው ጥራትና መጠኑን እያሻሻለ ለሀገር ጠቃሚና ገንቢ የሚሆኑ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን እያቀረበ መሆኑን ገልጸው የግብርና፣ የተፈጥሮና ቀመር እና የሕክምናና ጤና ሳይንስን የሚመለከቱ የጤና፣ የምግብ ዋስትና፣ የአየር መዛባት ችግሮችን በመለየት በሳይንስ የተደገፈ ጥናት በማቅረብ በዘላቂነት ኅብረተሰቡን ከችግሩ በማለቀቅ ሳይንስን መሠረት አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ ፕ/ር ተፈራ በላቸው ለዘላቂ ልማት የሳይንስ ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ያሉንን ሀብቶች አጠቃቀምን ከፍ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ልናረጋግጥ እንችላለን ብለዋል፡፡ የምግብ ዋስትናን በእንሰሳት ተዋጽኦ ብቻ ማረጋገጥ ስለማይቻል በእጽዋት መተካት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ ብዙ ሴክተሮች እነዚህን ችግሮች በመገንዘብ በፖሊሲዎቻቸውና በተለይ በምርምርና ልማት ዙሪያ ትኩረት እያደረጉ መሆኑን ፕ/ሩ ተናግረዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ እንደተናገሩት በሚቀርቡት የጥናት ውጤቶች ለይ ከምሁራን የሚሰጡ ሙያዊና ሳይንሳዊ አስተያየቶችና ትችቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸው ጥናቶቹ ወደ ማኅበረሰቡ ወርደው በተግባር የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እንዲችሉ ያግዛል፡፡ በተጨማሪም መሰል ዓውደ ጥናቶች መኖራቸው ምሁራኑ እርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና አብረው በጋራ መሥራት እንዲችሉ ይረዳል ብለዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከቀረቡት የምርምር ሥራዎች መካከል ሕጻናት በተወለዱ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ቀናት ውስጥ ስለሚሰጡ የምግብና የፈሳሽ ዓይነቶች ዙሪያ በመ/ር ነጋ ደገፉ የቀረበው አንዱ ሲሆን እንደ ጥናት አቅራቢው ንጥር ቅቤ፣ የፈላ ሻይ፣ ቡና ቅጠልና ውሃ የመሳሰሉትን ማኅበረሰቡ በተለምዶ አንጀት ያፀዳል በሚል የተሳሳተ ግምት ለሕፃናቱ ይሰጣል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕፃናት ለበሽታ በቀላሉ መጋለጥ፣ መቀጨጭና መቀንጨር ችግሮች ይዳረጋሉ፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ለእናቶች ግንዛቤ ማስጨበጥና በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ማድረግ እንደሚገባ በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡

ሌላው የምርምር ጽሑፍ ንጥረ-ነገሮችን በመጠቀም ምግብን ማበልጸግ በሚል ርዕስ በመ/ርት ዋጋዬ ዓለሙ የቀረበ ሲሆን በጥናቱ ትኩረት የነበረው በቆሎና ማሽላን ማኅበረሰቡ በብዛት የሚጠቀም በመሆኑ ሁለቱን በማዋሃድ እንደ ቺፕስ ያለ ምግብን በዘመናዊ ማሽን በማዘጋጀት አብስሎ በመጠቀም በተለይ እናቶችና ሕጻናት እንዲመገቡ በማድረግ በዚንክና ብረት እጥረት ከሚመጡ የጤና እክሎች ማኅበረሰቡን ለመታደግ እንደሚቻል በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የመጡ መምህራንና ተመራማሪዎች፣ ከጋሞ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት መምሪያ፣ ከአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ተቋም፣ ከአርባ ምንጭ ሆስፒታልና ከከተማው ጤና ቢሮ የተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን 46 የምርምር ሥራዎች ቀርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ደይሬክቶሬት