- Details
በማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ እንዲሁም በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጆች አዘጋጅነት ‹‹ምርምር ለልማት›› በሚል መሪ ቃል ከሚያዚያ 30-ግንቦት 1/2007 ዓ/ም ለ3ኛ ጊዜ በዋናው ግቢ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የምርምር አውደ ጥናት ላይ ከ15 ዩኒቨርሲቲዎችና ምርምር ተቋማት በተወጣጡ ጥናት አቅራቢዎች 30 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል ፡፡
በዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ፋንታሁን ወልደሰንበት እንደገለጹት አውደ ጥናቱ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ተመራማሪዎች በወቅታዊ ችግሮች ላይ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንዲጠቁሙ የሚያግዝ ነው፡፡ በተጨማሪም ዓውደ ጥናቱ በዩኒቨርሲቲዎች መካከል የልምድ ልውውጥ በማድረግና የትብብር ምስረታዎችን በማጠናከር ረገድ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ጥናታዊ ጹሑፎቻቸውን ካቀረቡት መካከል በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ሙዑዝ ሃይሉ አንዱ ሲሆኑ የጥናታቸውም ርዕስ “ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ጋዜጦች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሰጡት ሽፋን” የሚል ነው፡፡ መገናኛ ብዙሃን ከሚዲያ መርሆች አንፃር ግድቡን አስመልክቶ እንዴት እደዘገቡት ማወቅን ዓላማ ያደረገው ጥናት በአንዳንድ ጋዜጦች ላይ የሚወጡ ዘገባዎች የናይል ተፋሰስ አገሮችን ጥቅምና ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ ሳይሆኑ በየአገሮቻቸው ፍላጎት ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ግድቡ ለኢትዮጵያም ሆነ ለጎረቤት ሀገሮች ያለው የልማት ጠቃሚነት የጎላ ስለሆነ ሚዲያዎች ሚዛናዊ ሽፋን መስጠት እንደሚገባቸው በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ (አማርኛ) ትምህርት ክፍል መምህርት ህሊና ሰብስበው ‹‹የግጭት አፈታት ሥርዓት ክዋኔ በጌዲኦ ብሄር›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረበች ሲሆን የብሄረሰቡ የግጭት አፈታት ሥርዓት ከማህበረሰቡ መልካም እሴቶች ጋር የተቆራኘ መሆኑን እና የማህበረሰቡን የእርስ በእርስ ግንኙነት እንደሚያጠናክር ዳስሳለች፡፡ የጥናት አቅራቢዋ በሰጠቸው ተጨማሪ አስተያየት በአውደጥናቱ የተለያዩ የምርምር ውጤቶች መቅረባቸው ወጣት ተመራማሪዎች ልምድ እንዲቀስሙ ያስችላል ብላለች፡፡
በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ዩኒቨርሲቲው በዋናነት ከሚያሳካቸው አበይት ተልዕኮዎች መካከል ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ ምርምሮች ማካሄድ አንዱ ስለሆነ ተመሳሳይ የምርምር ስራዎች በቀጣይም በሌሎች ኮሌጆች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል፡፡
- Details
የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሚያዝያ 16/2007 ዓ.ም በሁሉም ካምፓሶች በተደረገው የጧፍ ማብራት ሥነ-ሥርዓት ላይ በመገኘት በሊቢያ በ30 ኢትዮጵያውያን ላይ ISIS በተባለ አሸባሪ ቡድን እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ በ4 ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመውን ኢ-ሰብዓዊ ግድያ በጥብቅ አውግዟል፡፡
በዋናው ግቢ በህሊና ፀሎት የተጀመረውን ሥነ-ሥርዓት በከፈቱበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ እንደተናገሩት በሁለቱም ሀገራት በዜጎቻችን ላይ የተፈፀመው ኢ-ሰብዓዊና አሰቃቂ ግድያ የኢትዮጵያውያንን ልብ በሐዘን የሰበረና በከፍተኛ ሁኔታ ቁጣ የቀሰቀሰ ነው፡፡ ፕሬዝደንቱ የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያውያን መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡ በተጨማሪም ሀገራችን ኢትዮጵያ የምታደርገው የዴሞክራሲ ግንባታና ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሸባሪዎች ዕኩይ ዓላማቸውን ለመፈፀም በሚያቀርቡት ሃይማኖታዊ ሽፋን ሳንደናገር የፀረ ሽብርተኝነት አቋማችን ምንግዜም የፀና መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅብን አሳስበዋል፡፡
በሌሎቹም ግቢዎች የፕሬዝደንት ተወካዮች፣ የኮሌጅ ዲኖችና የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተወካዮች ለተጎጂ ወገኖች የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ መንግሥት ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉም ዜጋ ከጎን በመሆን የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በተለይም የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንትና ተወካዮቹ በሀገራችን ሠርተን የመሻሻል አማራጮች በርካታ ስለሆኑ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር በመውጣት የአሸባሪዎች ሲሣይ መሆን ሊያበቃ ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሽብርተኝነትን ከመታገል ጎን ለጎን ወጣቶች በሀገር ውስጥ የተፈጠሩና እየተፈጠሩ ያሉ የሥራ አማራጮችን አሟጠው እንዲጠቀሙና በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንዳይወጡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንፃር የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሽብር ድርጊቱን የሚያወግዙ የተለያዩ የሥነ-ጽሑፍ ዝግጅቶች ቀርበዋል፡፡ የሥነ-ሥርዓቱ ተካፋዮችም ‹‹አክራሪነትና ሽብርተኝነት የትኛውንም ኃይማኖት አይወክልም››፣ ‹‹አንድነታችንን አጠናክረን ሽብርተኝነትን እንዋጋለን››፣ ‹‹የአይኤስአይኤስ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን በጥብቅ እናወግዛለን›› የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን በመያዝና በጋራ ድምጽ በማሰማት ጧፍ እያበሩ በየግቢው በተዘጋጁ ቦታዎች የጥቃቱ ሰለባዎችን በማሰብ የእግር ጉዞ አድርገዋል::
- Details
የፎረሙ ውይይት በዋናው ግቢ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣የአስተዳደር ሠራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት ሚያዝያ 30 ተካሂዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ኮንፈረንሱን በንግግር በከፈቱበት ወቅት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ፎረም ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የፎረሙ ተሳታፊዎች ከመልካም አስተዳደርና ከትምህርት ጥራት አንፃር መሻሻል የሚገባቸውን አፈጻጻሞች በተመለከተ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ በሚያስችል መልኩ ውይይቱን እንዲያካሂዱ አሳስበዋል፡፡
ኮንፈረንሱ በዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል በትምህርት ክፍሎችና በኮሌጆች ደረጃ በተከታታይ በተደረጉ ውይይቶች ተለይተው የወጡ ችግሮችንና ድክመቶችን እንደየባህሪያቸው የአጭር፣ የመካካለኛ እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በማውጣት በዘላቂነት ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ የሁሉንም ኮሌጆችና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ሪፖርቱን ተከትሎ የሁሉም ኮሌጆች ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች አስተያየቶችን፣ ጥቆማዎችንና ጥያቄዎችን በመሰንዘር የመብራት፣ የኢንተርኔት፣ የውሃና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች አካባቢ የሚታዩትን ክፍተቶችና ከፍተኛ መሻሻሎች ገምግመዋል፡፡
ዲኖቹ ለአስተያየትና ጥቆማ ሰጪዎች ምስጋና በመቸር ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሠጡበት ወቅት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መምህራን የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ መደረጉን፣ የብቃት ችግር አለባቸው የተባሉ የአንዳንድ የውጭ አገር መምህራን ኮንትራት መቋረጡን እንዲሁም መምህራን የተማሪዎችን ፈተና በወቅቱ አርመው ውጤታቸውን የሚያሳዩበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ከትምህርት ክፍሎች ጋር በመተባበር እየተሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ የ1 ለ 5 አደረጃጀት በሁሉም ክፍሎች ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውን የሚያስችልና ክትትል የሚያደርግ ከአስተዳደር ሰራተኞች፣ ከመምህራንና ከተማሪዎች የተወከለ የሱፐርቪዢን ቡድን ተቋቁሞ ሥራ ላይ መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡
የሁሉም ኮሌጆች ዲኖች እንደተናገሩት ከተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም ከአስተዳደር ሠራተኞች የስኬት ማነቆ ሆነው የተለዩትን ችግሮች ለመቅረፍ በተቀመጠው መርሃ ግብር መሠረት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ሊፈቱ የታቀዱ ችግሮችን በተቀናጀ ጥረት ለመሻገር በርትተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡
ዶ/ር ፈለቀ ኮንፈረንሱን ሲያጠቃልሉ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ሊተገበሩ የታቀዱ እንዲሁም እስከአሁን መፍትሔ ያልተሰጣቸው የተወሰኑ የአጭር ጊዜ ተግባራት በቀጣይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራባቸው በመግለጽ የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ የትምህርት ልማት ሠራዊት ግንባታን ይበልጥ በማጠናከር የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ሁሉም ባለድርሻዎች በቅንጅት እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡
- Details
በዩኒቨርሲቲው የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ በስሩ በተከፈቱ 7 የትምህርት መስኮች ዘርፈ ብዙ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በእንስሳት፣ በእፅዋት እና ደን ሳይንስ የትምህት ዘርፎች የሚካሄዱት ምርምሮች ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የዕፅዋት ሣይንስ ትምህርት ክፍል ተጠሪ አቶ ኪያ አደሬ እንደገለጹት በትምህርት ክፍላቸው ጥራጥሬና ሰብሎችን አራርቆ መዝራት፣ ተፈጥሯዊና ዘመናዊ ማዳበሪያ አጠቃቀምን ጨምሮ የተለያየ እንክብካቤ በመስጠት የምርታማነት ዕድገትን ለመጨመር የሚያስችሉ ዘዴዎችን ለመለየት በትጋት እየተሰራ ነው፡፡
በዋናው ግቢ የእርሻ ምርምር ማሳያ ላይ እየተካሄደ ያለውን የሸንኮራ አገዳ ምርምር አስመልክተው ፕሮፌሰር አብዱል ቀይም ከሃን እንደተናገሩት ዩ ኤስ ኤን ጨምሮ ከተለያዩ 8 አገሮች የተሰባሰቡ 16 ዓይነት የሸንኮራ አገዳ ምርጥ ዝርያዎች እየተጠኑ ነው፡፡ ለወደፊትም ለኦሞ ኩራዝ፣ ለወንጂና ለመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች የተሻለ ግብዓት እንዲሆን ምርምሩን ስኬታማ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል፡፡
የደን ሣይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮናስ ኡጎ በበኩላቸው ትምህርት ክፍላቸው የአካባቢውን የደን ሀብት ለማሳደግ የሚያስችሉና ከአካባቢው የአየር ንብረት ጋር ተዛማጅ የሚሆኑ የዛፍ ዝርያዎችን በማጥናት ችግኝ አፍልቶ ለዩኒቨርሲቲው ካምፓሶችና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የማድረስ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡ በዚህ ዓመት ከድሬዳዋ ተገዝቶ የመጣውን የእውነተኛ ኒም ዛፍ ችግኝ በማፍላት እስከ አሁን ከ14,000 በላይ ችግኞች የተሰራጩ ሲሆን በዘርፉ ቀጣይ ምርምሮችን በማካሄድ ከአንድ በላይ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ ዛፎችን ለማስተዋወቅና ለማላመድ አቅደን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
የእንስሳት ሣይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ሠይፉ ብርሃኑ በትምህርት ክፍላቸው ምርጥ የወተት ላም ዝርያዎችን ከአካባቢው ዝርያዎች ጋር የማዳቀል ሥራ በቅርቡ የሚጀመር መሆኑን በመጥቀስ የእንስሳት መኖ ዕፅዋትን በማላመድ ለምርጥ የወተት ላሞችና ለዶሮ እርባታ ሥራዎች ግብዓት እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የፕሮፌሰር ሰለሞን ‘chicken brooding box’ የተባለ ዘመናዊ የጫጩት ማሳደጊያ አጠቃቀም ጥናት እንደተጠናቀቀም ቴክኖሎጂው ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ይሆናል፡፡
የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ነጂብ መሐመድ እንደተናገሩት ኮሌጁ ከተቋቋመ ገና ሁለት ዓመት ብቻ ቢሆነውም እየሠራቸው ያሉት ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ ዲኑ በኮሌጁ ባሉት ሁሉም የትምህርት ክፍሎች በመምህራንና በተለይም በተመራቂ ተማሪዎች አበረታች ምርምሮች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልፀው የተጀመሩትና ሌሎችም አዳዲስ ምርምሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
- Details
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት በአባያ ክ/ከተማ በኩልፎ ቀበሌ ለተገኙ በርካታ አረጋዊያንና ወላጅ አጥ ሕፃናት የ2007 ዓ.ም የፋሲካ በዓልን በማስመልከት የምሳ ግብዣ አድርጓል፡፡
“የሰጪ እጅ ሁሌም ከላይ ነው” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን የምሳ ግብዣ ያሰናዱት የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ጌትነት ዓለሙና የተማሪዎች ዲስፕሊን ተጠሪ ተማሪ ታመነ ዳኘው ናቸው፡፡ ተማሪ ጌትነት ባደረገው ንግግር የአ/ም/ዩን ተማሪዎች ወክሎ ከታዳሚዎቹ መሃል በመገኘት በዓሉን ማክበሩ እንዳስደሰተውና ለወደፊትም በተመሳሳይ መልክና የበለጠ አቅም በመፍጠር በዓላትን በጋራ ለማሳለፍ እንደሚሠሩ ተናግሯል፡፡
በአባያ ክ ከተማ የኩልፎ ቀበሌ ወጣቶችና ስፖርት ዘርፍ ኃላፊ ወጣት ተክሌ ብርሃነገነት እና የአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽ ቤት ምኃላፊና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ ወጣት በላይ ግዛቸው የአምዩ ተማሪዎች ኅብረት ያደረገውን ድጋፍ አመስግነው ለወደፊትም መሰል ትብብርና በጋራ የመሥራቱ ልምድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ በዝግጅቱ መጨረሻም የአ ም ዩ ተማሪዎች ኅብረት ለተሳታፊ ስፖንሰሮች የተሰጠውን የምሥክር ወረቀት ወስዷል፡፡
በተመሳሳይም የአ/ም/ዩ ከፍተኛ የአስተዳደር አካላት በ5ቱም ካምፓሶች ከተማሪዎች ጋር በመሆን የፋሲካን በዓል በድምቀት አክብረዋል፡፡ በዋናው ግቢ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ከሌሎች የአስተዳደር አካላት፣ የተማሪዎች ፕሬዝደንትና የተማሪዎች ተወካይ ኮሚቴዎች ጋር በመገኘት በዓሉ ደማቅ እንዲሆንና ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳሉ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ድባብ ፈጥረዋል፡፡
በሌሎቹም ካምፓሶች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖችና የሥራ ክፍል ኃላፊዎች እንዲሁም የተማሪዎች ተወካዮች ከተማሪዎች ጋር በመሆን በዓሉ በልዩ ድምቀት እንዲከበር አድርገዋል፡፡