ዩኒቨርሲቲው ለ32ኛ ጊዜ 6,857 ተማሪዎችን በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በቅድመ ምረቃና በድኅረ ምረቃ ያሰለጠናቸውን 6,857 ተማሪዎች ሰኔ 29/2011 ዓ/ም አባያ ካምፓስ በሚገኘው አዳራሽ እና ሰኔ 30/2011 ዓ/ም በሣውላ ካምፓስ በድምቀት አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎች መካከል  4,434 ወንዶች ሲሆኑ 2,423 ሴቶች ናቸው ፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ተመራቂዎች የሥራ ዓለምን ሲቀላቀሉ ከዩኒቨርሲቲው በገበዩት እውቀት፣ ክህሎትና መልካም ሥነ-ምግባር መንግሥትና ህዝብ የአገሪቱን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እያደረገ ባለው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንዲሁም ራሳቸውን፣ ወገናቸውንና አገራቸውን ለማሳደግ እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ይናገር ደሴ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ ተማሪዎች በተለያየ መልኩ ወደ ሥራው ዓለም  ሲቀላቀሉ በአገራችን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን መልካም ተስፋ እየታየ ቢሆንም ተስፋውን የሚያደበዝዙ ችግሮች ይስተዋላሉ ያሉት ዶ/ር ይናገር ችግሮች እንዳይከሰቱና ከተከሰቱም በሰከነ ሁኔታ እንዲፈቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚሠራጩ ሀሰተኛ ወሬዎች ቦታ ሳይሰጡ ለአገራችን አንድነትና አብሮነት የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

የዕለቱ እንግዳና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ አባል ዶ/ር አብርሃም አላኖ በበኩላቸው የአንድ አገር ልማት ያለ ትምህርት መስፋፋት እውን ሊሆን እንደማይችል መንግሥት ተረድቶ ለከፍተኛ ትምህርት ፍትሃዊ መስፋፋትና ተደራሽነት በትኩረት ሲሠራ የቆየ በመሆኑ በዘርፉ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡ መንግሥትና የዘርፉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር አብርሃም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በአገሪቱ ከሚገኙ የመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በሁሉም መስኮች ቀዳሚ የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በዕድገት ላይ የምትገኝ አገር መሆኗን ያወሱት የክብር እንግዳው ከለውጡ ጋር ተያይዞ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉ ሁሉ ከፍተኛ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች የተጋረጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ የዕለቱ ተመራቂዎች ምክንያታዊ በመሆንና ከግለኝነት አስተሳሰብ በመውጣት ለማኅበረሳባችን ለውጥ ብሎም አገሪቱ ከገጠማት ፈተና እንድትወጣና የተጀመረው ለውጥ እውን እንዲሆን የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ከአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል 4 ነጥብ በማምጣት የሜዳልያና ዋንጫ ተሸላሚ የሆነው የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ተመራቂ እስማኤል ፈድሉ በሰጠው አስተያየት ጠንክሮ መሥራቱና ጊዜውን በአግባቡ መጠቀሙ ለስኬት እንዳበቃው ገልጿል፡፡ ማንኛውም ሰው በተሰማራበት መስክ ዓላማ በመሰነቅ በቁርጠኝነት ከሠራ ውጤታማ መሆን ይችላል ያለው ተሸላሚው አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ ጅምር በመሆኑ የትምህርት ደረጃውን በማሻሻል አገሩን በታማኝነትና በቅንንት እንደሚያገለግል ተናግሯል፡፡

3.98 በማምጣትና 43 A+ በማስመዝገብ በ2ኛነት የተሸለመው የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን ትምህርት ክፍል ተመራቂ ቃለአብ ወንድሙ ታሪኩ በዓላማ መንቀሳቀስና ተግቶ መሥራት ለስኬት ያበቃል ብሏል፡፡ ሰሚራ ዲልቦ አወል ከኮኦፕሬቲቭ አካውንቲንግ እና ኦዲቲንግ ት/ት ክፍል 3.94 ከሴቶች ከፍተኛውን ውጤት በማምጣት እንዲሁም ተመራቂ ዘሀራ ያሲን አማን ከኮምፒውተር ሣይንስ ት/ት ክፍል 3.92 በማምጣትና 16A+ በማስመዝገብ ልዩ የወርቅ ሀብል ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡

በዕለቱ ከየትምህርት ክፍላቸው 1ኛ ለወጡ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ሽልማት፣ ከኢንስቲትዩት፣ ከኮሌጅና ከት/ቤት 1ኛ ለወጡ ምሩቃን የወርቅ ሜዳልያ፣ ከኢንስቲትዩት፣ ከኮሌጅና ከት/ቤት 1ኛ ለወጡ  ሴት ምሩቃን ልዩ ሽልማት፣ በአጠቃላይ ሴት ምሩቃን መካከል ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበች ምሩቅ የአንገት ሐብል ሽልማት እንዲሁም ከአጠቃለይ ምሩቃን ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበው ምሩቅ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት