የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በ‹‹አረንጓዴ አሻራ ቀን›› ከ19 ሺ በላይ ችግኞችን ተከለ

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሐምሌ 22 በተደረገው ‹‹የአረንጓዴ አሻራ ቀን›› በቤሬ ተራራና በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ካምፓሶች ከ19 ሺ በላይ ችግኞችን በመትከል አሻራውን አኑሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተከላው ባሻገር 75 ከመቶ በላይ ችግኞችን ለከተማው በማቅረብና በወዜ ተራራ ላይ ከ13 ሺ በላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን በማዘጋጀት የድርሻውን አበርክቷል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በነበረው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ከተጠበቀው በላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉን ገልፀው ችግኞቹ እንዲፀድቁ በተቀናጀ ሁኔታ አስፈላጊው እንክብካቤና ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡ ባልተመቻቸ ሁኔታም ቢሆን ለአገራዊ ጥሪው በነቂስ በመውጣት ተሳትፎ ላደረገው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በዩኒቨርሲቲው ስም ላቅ ያለ ምስጋናም አቅርበዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ የተተከሉ ችግኞችን በእንክብካቤ የምናሳድጋቸው ከሆነ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በዚህ ክረምት እንደ አገር 4 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

አካባቢን መጠበቅ የሥልጡን ዜጋ ምልክት ነው ያሉት  ዶ/ር ስምዖን ሥራው የዘመቻ ሥራ ብቻ ሳይሆን እንደ ልምድ ሁል ጊዜም መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ስምዖን እንደ ዩኒቨርሲቲ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ማድረግ ትልቁ የቤት ሥራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ ሥራው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የሥራ አካልና የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ በልማት ሥራዎች ጽ/ቤት አማካይነት በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

በችግኝ ተከላው የተሳተፉ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አካላት በሰጡት አስተያየት የዚህ ታሪካዊ ቀን አካል በመሆን አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖራቸው ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡

በችግኝ ተከላው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ የክረምት ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞችን ጨምሮ ከ11 ሺህ በላይ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በመርሃ ግብሩ ተሳትፏል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት