ለዩኒቨርሲቲው ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራንና የፒ ኤች ዲ ተማሪዎች ‹‹Multi-Physics Modeling and Simulation Opportunities and Challenges›› በሚል ርዕስ እንግሊዝ አገር በሚገኘው ማንችስተር ዩኒቨርሲቲ የውኃ ዘርፍ መምህርና ተመራማሪ በሆኑት የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ምሩቅ ዶ/ር ሮቤል ጥላዬ አማካይነት ከሐምሌ 11-13/2011 ዓ/ም የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን ማኅበር፣ በውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና በሬጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን በውኃ ግድቦች አስተዳደር፣ በወንዝ ተፋሰስ አስተዳደር፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሞዴሎች እንዲሁም በተለያዩ የምልከታ መሣሪያዎች ዙሪያ ያተኮረ ነው፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

ሥልጠናውን የሰጡት ዶ/ር ሮቤል ጥላዬ ዩኒቨርሲቲው በውኃ ሀብት ምህንድስና የልህቀት ማዕከል በመሆን በአገሪቱ በሚሠሩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የራሱን ሚና እንዲወጣና የማማክር አገልግሎት እንዲሰጥ ሥልጠናው ጉልህ ሚና ያበረክታል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ሮቤል በቀድሞው አርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሀይድሮሊክ ምህንድስና እንዳገኙ ገልጸው በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው ቆይታ ጥሩ ጊዜ እንዳሳለፉና በርካታ አዎንታዊ ለውጦችን እንደታዘቡ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ባላቸው ዕወቅት ዩኒቨርሲቲውን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረው በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን ለዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የውኃ ቴክኖሎሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል እንደገለፁት ሥልጠናው በተለይ መምህራን ያላቸውን ዕውቀት ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር እንዲቃኙ እንዲሁም ተማሪዎቻቸውን ለማስተማር የሚያዘጋጇቸውን የማስተማሪያ ግብዓቶች አሁን ካለው ሁኔታ ጋር በማዛመድ እንዲያዘጋጁ በማድረግ የተሻለ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲኖር ያግዛል፡፡ ሥልጠናው ከመምህራኑ ባሻገር ለውኃ ሀብት ምርምር ማዕከል ተመራማሪዎችና ሠራተኞች ጭምር የተሰጠ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አብደላ ይህም በማዕከሉ በሚሠሩ የምርምር ሥረዎች ጥራትና ውጤታማነት ላይ ጉልህ ድርሻ ያበረክታል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት የአልሙናይ ተባባሪ ሬጅስትራር ዶ/ር ሐብታሙ እንድሪስ በበኩላቸው የተሰጠው ሥልጠና የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን ማኅበር ከሚሠራቸው ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው መሰል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡ ሥልጠናዎቹ በገንዘብ ሲተመኑ ዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛ ወጪ ሊያስወጡ እንደሚችሉ የተናገሩት ዶ/ር ሐብታሙ ሥልጠናውን በነፃ በመስጠት አርኣያነት ያለው ተግባር ለፈጸሙት ዶ/ር ሮቤል እንዲሁም ለቀድሞ ምሩቃን ማኅበር ፕሬዝደንት ለአቶ ኤርሚያስ ዓለሙ ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በሥልጠናው ከአዳዲስ አሠራሮችና ቴክኖሎጂዎች ጋር መተዋወቃቸውን ገልፀው ይህም ለመማር ማስተማርም ሆነ ለምርምር ሥራዎች አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት