ቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮጀክት በ4 ወረዳዎች በሚገኙ የሙከራ ጣቢያዎች የመስክ ምልከታ አካሂዷል

ቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮጀክት በተለያዩ 4 ወረዳዎች በሚገኙ የሙከራ ጣቢያዎች ከሐምሌ 15-19/2011 ዓ/ም የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡ በምዕራብ አባያ ወረዳ በያይቄና በዛላ ጉትሻ ቀበሌዎች የአደንጓሬ፣ የበቆሎና ድንች እንዲሁም በደራሼ ወረዳ በሆልቴ፣ በቁጫ ወረዳ በጋሌ፣ በዛላ ወረዳ በሜላ ባይሳ ቀበሌዎች በተመሳሳይ የበቆሎና የማሽላ  የሙከራ ሥራዎች ምልከታ ተደርጎባቸዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንደገለፁት የምግብ ዋስትና ችግር ባለበት አካባቢ የአካባቢውን የአየር ሁኔታና በሽታን ተቋቁመው ማህበረሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ ዝርያዎችን አርሶ አደሩን ባሳተፈ መልክ  በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ የሆኑትን መለየት መቻሉ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ በፕሮጀክቱ የተሰራው ሥራ አበረታች ነው፡፡

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የተሻሻሉ ምርጥ ዝርያዎችን ለመለየት በተካሄደው ሙከራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገኘው ውጤት ለምርትና ምርታማነት መሻሻል አዎንታዊ አስተዋፅዖ ያለው በመሆኑ በቀጣይ ዝርያዎቹን ለአርሶ አደሩ የማዳረስ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

የቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ የፕሮጀክቱ ዓላማ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የሴፍቲኔት ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን ገቢ ማሳደግ እንደመሆኑ አሁን ላይ በተደረገው ሙከራ በአርሶ አደሮቹ የተለዩትን ምርጥ ዝርያዎች በቀጣይ የማከፋፈል ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት አቶ ካንኮ ጩንታለ በፕሮጀክቱ እየተሞከረ ያለው ሥራ በዋናነት አሁን ላይ የተለዩትን ምርጥ ዝርያዎች ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመረባረብ ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ በሰጡት አስተያየት በፕሮጀክቱ  አማካይነት  የተለዩት ምርጥ ዝርያዎች የአካባቢውን አየር ሁኔታ የሚቋቋሙና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱና የተሻሻሉ በመሆናቸው ወቅቱን በጠበቀ የፀረ-ተባይ ማጥፊያ ኬሚካሎች አጠቃቀም ውጤታማ መሆን እንችላለን ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ በተከናወነው ሙከራ ከአደንጓሬ ‹‹ሀዋሳ ዱማ››፣ ከድንች ‹‹በለጠ››፣ ከበቆሎ BH547 እንዲሁም ከማሽላ ‹‹መልካም›› የተሰኙ ዝርያዎች የተሻሉ ዝርያዎች ሆነው ተገኝተዋል፡፡

በመስክ ምልከታው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት፣ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የፕሮጀክቱ ኃላፊና ባለሙያዎች፣ የየወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎችና የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት