የዩኒቨርሲቲው የ2011 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2012 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ በዩኒቨርሲቲው ካውንስል ሐምሌ 24 እና 25/2011 ዓ/ም ተገምግሟል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የ2011 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2012 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ በዩኒቨርሲቲው ካውንስል ሐምሌ 24 እና 25/2011 ዓ/ም ተገምግሟል፡፡
በሪፖርቱ እንደተጠቆመው ሀገራዊ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ውጤቶችን ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የማስጨበጥ ሥራ በስፋት መሰራቱ፣ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የዩኒቨርሲቲ-ማህበረሰብ ትስስር ፎረም አደረጃጀቶችን ለማጠናከርና በየደረጃው የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ውይይት መካሄዱ፣ ዩኒቨርሲቲው ከኢንዱስትሪዎች ጋር የሚኖረውን መስተጋብር ለመጠበቅና ለማሻሻል እንዲያስችል 17 ኢንዱስትሪዎችንና 13 ቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ያሳተፈ ፎረም መዘጋጀቱ፣ የሜካኒካልና ፕሮዳክሽን ኢንጂነሪኒግ ፋካሊቲ ፕሮግራምን የማስተዋወቅ ወርክሾፕ መዘጋጀቱ፣ በምርምር ዘርፍ 1 አለም አቀፍና 5 ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት መካሄዳቸውና ሳይንሳዊ ውይይትና ግምገማ መደረጉ በሪፖርቱ የተጠቀሱ መልካም አፈፃፀሞች ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው ነፃ የሕግ የአገልግሎት ሰጪ ማዕከላት ለ3708 አቅመ-ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች የምክር፣ የክስ አቤቱታ አፃፀፍና የጥብቅና አገልግሎት መስጠቱ፣ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለደረጃ ዕድገት ለበቁ 16 መምህራን የረዳት ፕሮፌሰርነት እንዲሁም ለ9 መ/ራን የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መሰጠቱ፣ ዩኒቨርሲቲው ከLucy Consulting Engineers plc ጋር ባደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ለርቀት ትምህርት ተማሪዎች የሚሰጡ ሞጁሎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ለተማሪዎች በቀላሉ እንዲያገኙት መደረጉ፣ ዩኒቨርሲቲውን ለተቀላቀሉ 214 አዳዲስ መምህራን የማስተማር ክህሎት ስልጠና መሰጠቱና ሌሎች በዓመቱ የተከናወኑ ተግባራት በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የተመራቂዎችን ወደ ሥራ የመቀላቀል ደረጃ ከፍ ማድረግ፣ የምርምር ሥራ ውጤቶችን፣ የተላመዱና የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ማሸጋገር፣ ተቋሙን ከኦዲት ግኝት የፀዳ እንዲሆን ማድረግ፣ የገቢ ማመንጫ አማራጮችን በማበራከትና አሰራሮችን በማሻሻል ገቢን ማሳደግ፣ የመደበኛና የካፒታል በጀት አጠቃቀምን ማሻሻል፣ የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ፎረሞችን በማጠናከር ከተማሪዎች፣ ከመምህራንና ድጋፍ ሰጪ የአስተዳደር ሰራተኞች ጋር ውይይቶችን በማካሄድ ግብአት በመውሰድ ክፍተቶችን ማስተካከል ዩኒቨርሲቲው በቀጣዩ በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸው በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡
የተማሪዎች ሞባይልና የላፕቶፕ ኮምፕዩተር በሌቦች መዘረፍ፣ በ2 ተማሪዎች መካከል የሚፈጠር አለመግባባትን በማስፋት የዩኒቨርሲቲውን ሠላም የማደፍረስ ሙከራዎች መደረጋቸው፣ ከዩኒቨርሲቲው ካምፓሶችና  ከስራ ስፋት የተነሳ የተሸከርካሪ ዕጥረት ችግር፣ የአስተዳደር ሠራተኞች የነጥብ ምዘና ሥርዓት (JEG) ምደባ ረዘም ያለ ጊዜ መውሰድ የመማር ማስተማሩንና ሌሎች የስራ እንቅስቃሴዎች የተፈታተኑ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በውይይቱ ማጠቃለያ እንደገለፁት በቀጣይ የበጀት ዓመት ካለፈው ስህተቶችና ደካማ አፈፃፀሞች ትምህርት በመወሰድ  በተለይ የትምህርት ጥራት፣ ምርምሮችን ማጠናከር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትን በማስፋፋት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በማጠናከር ተቋሙን ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር በትኩረት መስራት እንደሚገባ አበክረው አሳስበዋል፡፡
ከሪፖርቱ ባሻገር የ2012 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የማሻሻያ ሀሳብ ግብዓቶችም ተሰብስበዋል፡፡ በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ አመራሮችና በየደረጃው ያሉ የካውንስል አባላት ተሳትፈዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት