አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የደጋ ኦቾሎ ቀበሌን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ አደረገ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በደጋ ኦቾሎ ቀበሌ ሲያከናውን የቆውን የንጹህ መጠጥ ውሃ መስመር ጥገናና የማስፋፋያ ፕሮጀክት አጠናቆ የዩኒቨርሲቲው፣ የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ እንዲሁም የቀበሌው አመራሮች በተገኙበት ሰኔ 20/2012 ዓ/ም በይፋ አስረክቧል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የፕሮጀክቱን አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት የደጋ ኦቾሎ ቀበሌ በ1972 ዓ/ም በካቶሊክ ቤተክርስትያን አማካኝነት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆን መቻሉን አስታውሰው ሆኖም ግን የተዘረጋው የውሃ መስመር ያለምንም ጥገናና ዕድሳት ለ38 ዓመታት በመቆየቱ አገልግሎት ያቆመ በመሆኑ የአካባቢው ማኅበረሰብ ለችግር መዳረጉን በመጥቀስ ዩኒቨርሲቲው ችግሩን እንዲፈታ የቀበሌው አስተዳደር በሐምሌ ወር 2010 ዓ/ም ጥያቄ ማቅረቡን አስታውሰዋል፡፡ ከቀበሌው የቀረበውን ጥያቄ መሠረት በማድረግ የነዋሪዎችን የውሃ ችግር አጥንቶ ተጨባጭ መፍትሄ የሚያመጣ ቡድን ተዋቅሮ ጥናት በማድረግ ጊዜያዊና ዘላቂ የመፍትሄ አቅጣጫ ለዳይሬክቶሬቱ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት ጊዜያዊ መፍትሄ ተብለው የቀረቡትን የተበሳሱ የብረት ቱቦዎችን በኤችዲፒኢ (HDPE) በመቀየርና ምንጩን የማፅዳት ሥራ ተሠርቶ ህዝቡ ለብዙ ጊዜያት ያጣውን የቧንቧ ውሃ በ2011 ዓ/ም መስከረም ላይ አገልግሎት እንዲጀምር ተደርጓል፡፡ በፕሮጀክቱ 2ኛ ምዕራፍ በእርጅና የተነሳ የተበሳሱትን የብረት ቱቦዎችንና ታንከሮችን በኤችዲፒኢ (HDPE) እና ፋይበር ግላስ ታንከር በመቀየር እንዲሁም ተጨማሪ ሁለት የውሃ ምንጮችን የማጎልበትና ውሃ ባልተደረሰባቸው መንደሮች ተጨማሪ 11 የውሃ ቦኖዎችን መሥራት መቻሉን ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ 560 አባወራዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ተክሉ ውሃውን በየመንደሩ ለማዳረስ ይረዳ ዘንድ የ5 ኪ.ሚ አዲስ የመስመር ዝርጋታም ተደርጓል ብለዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋሞ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ እንድሪያስ እንዲሁም የአ/ምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ መስፍን ደነቀ የተገኙ ሲሆን በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክትም ዩኒቨርሲቲው ይህን የመሰለ ትልቅና የማኅበረሰቡን ችግር የሚቀርፍ ፕሮጀክት የራሱን ባለሙያዎች ተጠቅሞ ሠርቶ በማስረከቡ በዞኑና በወረዳው ህዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ መሰል የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግሮች በሌሎች አካባቢዎችም በስፋት የሚስተዋሉ በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን እጅግ አበረታች ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አመራሮቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ የማኅበረሰቡን የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ሥራ ተሳታፊ የሆኑት በዩኒቨርሲቲው ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት የውሃ አቅርቦትና አካባቢ ኢንጂነርንግ ፋካልቲ መ/ር ኢ/ር ዳዊት አሻግሬ በበኩላቸው በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የተከናወነው ፕሮጀክት በዩኒቨርሲቲው ኢንጂነሮችና ባለሙያዎች መሠራቱ የፕሮጀክቱን ወጪ በእጅጉ መቀነስ የቻለ ሲሆን መሰል ፕሮጀክቶች በሚሰሩ ጊዜ የሚገጥሙ መጓተቶችን፣ ማጭበረበሮችንና የጥራት ችግሮችን መቅረፍ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድና ችግሮች በኋላ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ የአካባቢው ማኅበረሰብ ሲጠቀም በማየታቸው ማኅበረሰብን ማገልገል ምን ያህል ውስጣዊ ደስታ እንደሚሰጥ እንዲገነዘቡ እንዳስቻላቸው የተናገሩት ኢ/ር ዳዊት የአካባቢው ማኅበረሰብም ፕሮጀክቱን በጥንቃቄ እንዲጠብቀው አሳስበዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በርከት ያሉ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በተለየዩ የዩኒቨርሲቲው መዳረሻ አካባቢዎች እየሠራ መሆኑን ገልፀው በዕለቱ ተመርቆ ለደጋ ኦቾሎ ማኅበረሰብ የተሰጠው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የዚሁ ሥራ አካል ነው ብለዋል፡፡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ የመጨረሻችን አይደለም ያሉት ዶ/ር ስምዖን ገጠር ላይ ያተኮሩ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በቀጣይ የ10 ዓመት ዕቅዳችን ሥር በማካተት በስፋት የምንሠራው ይሆናል ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ መዝጊያ ንግግር የደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ፕሮጀክቱ በስኬት ተጠናቆ አገልግሎት ላይ እንዲውል የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ክፍሎችና ባለሙያዎች በዩኒቨርሲቲው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በቀላል ወጪ ትልቅ የማኅበረሰብን ችግር መቅረፍ እንደሚቻል ትምህርት የወሰድንበት ነው ያሉት ዶ/ር ዳምጠው የአካባቢው ማኅበረሰብም ከዚህ በኋላ ፕሮጀክቱን ተረክቦ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ እያደረገ እንዲጠቀም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በቀበሌያቸው የነበረው ውሃ በመበላሸቱ ምክንያት የወንዝ ውሃ በመጠጣት ለተለያዩ የጤና ችግሮች ሲዳረጉ እንደነበር አስታውሰው ዩኒቨርሲቲው የቀረበውን የደጋ ኦቾሎ ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ጥያቄ በመቀበል እኛ ከታሰበው በላይ አስፍቶ ስለመለሰ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ፕሮጀክቱን እንደ ግል ንብረታቸው ሁሉ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የደጋ ኦቾሎ የንጹህ መጠጥ ውሃ መስመር ጥገናና የማስፋፋያ ፕሮጀክት ሥራ ከ900 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት