ለአርባ ምንጭና ሳውላ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤች የዴስክ ቶፕ ኮምፕዩተሮች ድጋፍ ተደረገ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንግሊዝኛ ቋንቋን የማስተማር ሥነ-ዘዴን ከICT ጋር አቀናጅቶ ለማስተማርና ለማሻሻል የሚረዱ 25 ኮምፕዩተሮችን ለአርባ ምንጭና ሳውላ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤቶች ሰኔ 15/2012 ዓ/ም አስረክቧል፡፡

ለት/ቤቶቹ የተደረገው ድጋፍ ዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋን የማስተማር ሥነ-ዘዴን ለማሻሻል ከተለያዩ የICT መሣሪያዎች ጋር አቀናጅቶ መጠቀም በሚል የቀረፀው ፕሮጀክት አካል ሲሆን ለኮምፕዩተሮቹ ግዥ ዩኒቨርሲቲው 675 ሺህ ብር ወጪ አድርጓል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በዩኒቨርሲቲያችን ተግባራዊ እየተደረጉ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል የእንግሊዝኛ ቋንቋ የማስተማር ሥነ-ዘዴን ለማሻሻል የሚሰራው አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ፕሮጀክቱ የትምህርት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በማድረግ የትምህርት አሰጣጡ እንዲሻሻል ያግዛል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ዩኒቨርሲቲው ወደ ልህቀት ማዕከልነት ለማሸጋገር እየሠራ በሚገኝባቸው 3 ት/ቤቶች ሲሆን በቀጣይ ፕሮጀክቱም ሆነ መሰል ድጋፎች በሌሎች ት/ቤቶች ላይ በስፋት ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ ኃላፊ ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ፕሮጀክቱ በዋናነት በአርባ ምንጭ፣ ሳውላና የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤቶች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ የቆየ ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደትም ት/ቤቶቹ ያላቸው የICT መሠረተ ልማት ምን እንደሚመስል እንዲሁም በየት/ቤቱ ያሉ መምህራን የተለያዩ የICT መሳሪያዎችን የመጠቀም ክሂሎት ያለበትን ደረጃ ለመለየት የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የመምህራኑን የICT መሳሪያዎችን አጠቃቀምና ክሂሎት ለማሻሻልና ለማጎልበት የሚረዱ የተለያዩ ሥልጠናዎች ከየት/ቤቱ ለተወጣጡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን ለ64 ሰዓት መሰጠቱን ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

ለት/ቤቶቹ የተደረገው የኮምፒዩተር ድጋፍ ት/ቤቶቹ ያላቸውን አቅም መሠረት አድርጎ የተሰጠ ሲሆን በቀጣይ በየት/ቤቱ በመንቀሳቀስ ለመምህራኑ በማስተማሪያ መፃህፍት ውስጥ ያሉትን የትምህርት ይዘቶች እንዴት ባለ መንገድ ከተለያዩ የICT መሳሪያዎችና ሶፍትዌሮች ፌስቡክና ጎግል ዶክ የመሳሰሉ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ማስተማር እንዲችሉ ሥልጠና የሚሠጥ ይሆናል ብለዋል፡፡ የተደረገው የኮምፒዩተር ድጋፍ ለዚህ ሥልጠናም ሆነ ሥራውን በቀጣይ ለማስቀጠል ይረዳል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት ር/መ/ር አቶ ስለሺ ካሳ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም በርካታ የቁሳቁስና የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ለት/ቤታቸው ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀው አሁን ላይ የተደረገውም የኮምፒዩተር ድጋፍ የት/ቤታቸው የእንግሊዝኛ መምህራን ከዚህ ቀደም የወሰዱትን ሥልጠና ወደ ተግባር ቀይረው እንዲጠቀሙ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን በት/ቤቱ ስም ያቀረቡት ር/መ/ሩ በቀጣይም መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና በት/ቤታቸው ተበላሽተው ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ኮምፒዩተሮች ተጠግነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ቢረዳን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት