የ82 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ በሕይወት ዘመናቸው ያነበቧቸውን የተለያየ ይዘት ያላቸውን 72 መፅሐፍት ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አበረከቱ

የ82 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አቶ ያቻ ያና በሕይወት ዘመናቸው ያነበቧቸውን የተለያየ ይዘት ያላቸውን 72 መጽሐፍት ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አበረከቱ፡፡

ከ1953 ዓ/ም ጀምሮ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ በመምጣት በከተማው በሚገኘው በእርሻ ልማት ውስጥ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በጡረታ እስከ ተገለሉበት ጊዜ ድረስ ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ያቻ ያና በሕይወት ዘመናቸው ምንም ዓይነት የመደበኛ ትምህርት ዕድል አላገኙም፡፡ ‹‹መደበኛ ትምህርት አለመማሬ ማንበብና መፃፍ እንዳልችል አላገደኝም›› የሚሉት አቶ ያቻ የግላቸውን ጥረት በማድረግና የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ማንበብና መፃፍ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

በሕይወት ዘመናቸው በርካታ መፅሐፍትን ማንበባቸውን የሚናገሩት አቶ ያቻ አሁን ላይ ዕድሜያቸው እየገፋ በመሆኑ ተማሪዎች መፅሐፍቱን እንዲያነቧቸውና በቀጣይነት እንዲጠቀሙ በማለም ለዩኒቨርሲቲው ለመስጠት እንደተነሳሱ ተናግረዋል፡፡ ባደረጉት በጎ ሥራም እጅግ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ አቶ ያቻ ያና በራሳቸው ተነሳሽነት ያደረጉት የመፅሐፍት አበርክቶ የሚያስመሰግንና አርአያነት ያለው የበጎ ፈቃድ ተግባር መሆኑን ገልፀው ግለሰቡ ላበረከቱት ስጦታ በዩኒቨርሲቲው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አሁን ላይ ያለው ትውልድ የተሻሉ የንባብ አማራጮችና ዕድሎች ቢኖሩትም የንባብ ባህሉ አነስተኛ ስለሆነ ትውልዱ ከእኝህ አባት ልምድና ጥረት ትምህርት ሊወስድ ይገባል ብለዋል፡፡

በማኅበረሰብ አገልግሎት የበጎ አድራጎትና ነፃ ፈቃድ አገ/ት ማ/ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፍቅርተ ስዩም በበኩላቸው አቶ ያቻ ለዩኒቨርሲቲው ያበረከቷቸውን መፅሐፍት በአግባቡ በማስቀመጥ ትውልዱ እያነበበ እንዲጠቀማቸውና ግለሰቡን እንዲያስታውሷቸው እናደርጋለን ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት