ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት የተላለፈ መልዕክት

ውድና የተከበራችሁ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች፣ አመራር አካላት፣የአስተዳደር ሠራተኞችና የቴክኒክ ባለሙያዎች በሙሉ
የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሶ የመጀመሪያዉ ዙር የዉሃ ሙሌት በመጠናቀቁ እንኳን ደስ ያለን !!!

ይህ ግድብ እንደ ስሙ የኢትዮጵያን ህዳሴ በማረጋገጥ ህዝቦቿን ወደ ብልጽግና በማምጣት የድህነትና የጉስቁልና ኑሮን የሚቀንስ ብሎም የሚያስወግድ የኢትዮጵያ ታላቅ ፕሮጀክት ነዉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅም ግዙፍ ጉዳዮችን መፈጸም እንደሚችሉ ለዓለም የበለፀጉ አገሮችም ጭምር በጉልህ የሚያስረዳ ክንውን ነዉ፡፡ ለኢትዮጵያዊያን ለራሳችን ደግሞ የእንችላለን መንፈስ የሚያጎለብት ፍጻሜ ነዉ፡፡

እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ በግድቡ ግንባታ ስኬት ጉልህ የሆነ አሻራዉን ሲያሳርፍ ቆይቷል፡፡ ተማሪዎች ከምግብ ባጀታችሁ ቀንሳችሁ መስጠት፣ ቶምቦላና ፒን ካርድ በመግዛት እንዲሁም ገንቢ ሃሳቦችን በማስተላለፍ አስተዋፅዖዋችሁ ጉልህ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደዚሁም መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች በተደጋጋሚ የወር ደመወዛችሁን በመስጠት፣ በልዩ ልዩ ገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች ሁሉ በመሳተፍ እና ስለግድቡ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ መልዕክት በማስተላለፍ የተጫወታችሁት ሚና በግድቡ አፈፃፀም ታላቅ አሻራ ለኢትየጵያ ብልጽግና ያበረከታችሁ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ እንኳን ደስ አለን፡፡

የግድቡ ሥራ በ2003 ዓ.ም በተጀመረበት ወቅት በየአካባቢዉ ሕዝብ የድጋፍ አስተያየት ሲያቀርብ በቴሌቪዥን ስከታተል ከየት አካባቢ እንደሆነ የማላስታውሰው አንድ ወጣት ሲገልጽ “እኔ ለዚህ ግድብ ሥራ የምሰጠዉ ነገር ማግኘት ካልቻልኩኝ ራሴ እንደ አንድ ድንጋይ ወይም ብሎኬት ሆኜ በግድቡ ተካትቼ እገደበላሁ” ብሏል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዚህ ግድብ መሳካት ያለው ምኞት ተመሳሳይ ነው፡፡

አሁን በመጨረሻዉ ምዕራፍ ላይ ግንባታውን በፍጥነት አጠናቀን ወደ ሙሉ አገልግሎት ለማስገባት ጀግናዉ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሻለቃ ኃይለ ገብረ ስላሴ የ5 ሺ እና የ10 ሺ ሩጫ ሲወዳደር በመጨረሻው ዙር ሩጫ ሂደት ላይ ለራሱ አለ የተባለዉን አካላዊ፣ አእምሮኣዊና መንፈሳዊ ተስጥዖውንና አቅሙን በሙሉ ተጠቅሞ አሸናፊ ሲሆን እንደቆየ ሁሉ እኛ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ለህዳሴዉ ግድብ ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንትጋ፡፡ ይህ ሲሆን በየጊዜው በግድቡ ዙሪያ በሬ ወለደ ዓይነት ምክንያት እየፈጠሩ ለመንግስትና ዘርፉን እየመሩ ለሚገኙ ኃላፊዎቸና ባለሙያዎች ውድ ጊዜያቸው እንዲባክን የሚያደርጉ አንዳንድ የውጭ አካላት መልካም ያልሆነ አመለካከትና አስተሳሰብ የሚቆም ይሆናል፡፡

በመሆኑም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ በሙሉ ግድቡን ለማጠናቀቅ በሚተላለፉ ጥሪዎች እንደበፊቱ ሁሉ እንዲንሳተፍ በአክብሮት እገልጻለሁ፡፡ ሠላምና ብልጽግና ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ይሁን!!

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት