አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከከተማው 3 ቀበሌያት ለተወጣጡና  ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው 250 አባወራዎችና እማወራዎች ለ2ኛ ጊዜ የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብር ሰኔ 3/2012 ዓ/ም አካሂዷል፡፡

መርሃ ግብሩ በዋናው ግቢ የውሃና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች እንዲሁም በኢትዮ- ፊሸሪ ኮንዶሚኒየም የሚኖሩ መምህራን ከግንቦትና ሰኔ ወር ደምወዛቸው በማዋጣት ያከናወኑት ነው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

በመርሃ ግብሩ ላይ  መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ  የዩኒቨርሲቲው መመህራን እንደ ሀገር ‹‹ማዕድ ማጋራት›› በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የተላለፈውን ጥሪ በመቀበል በራሳቸው ተነሳሽነት ከወር ደመወዛቸው በመቀነስ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን መርዳት መቻላቸው የሚያስመሰግንና አርአያነት ያለው ተግባር ነው ብለዋል፡፡ መሰል ተግባራትም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በሁሉም ካምፓሶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለችግር የተዳረጉ 450 አባወራዎችንና እማዎራዎችን በ1ኛው ዙር መደገፋቸውን በመጥቀስ በ2ኛውም ዙር መርሃ-ግብር ለ250 ቤተሰብ ኃላፊዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የምግብ እህልና ዘይት ድጋፍ የተደረገ ሲሆን መሰል ሥራዎችም ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የውሃና ቴክኖሎጂ ኢንስትዩቶች ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች ዶ/ር አብደላ ከማልና ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው ወረርሽኙ አሉታዊ ተጽዕኖ የፈጠረባቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች መርዳትና መደገፍ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው ከዚህ በኋላም የሁለቱን ኢንስቲትዩቶች መምህራንና ሠራተኞች በማስተባበር መሰል ድጋፍ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት እርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ ግድ መሆኑን በአጽንዖት  የተናገሩት ዳይሬክተሮቹ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ መሳተፍ ከፍተኛ የውስጥ እርካታን የሚሰጥ ተግባር በመሆኑ  በዩኒቨርሲቲው በክረምቱ  ለማከናውን በታቀዱ የደም ልገሳ፣ የችግኝ ተከላ፣ የማዕድ ማጋራትና የአቅመ ደካማ ቤቶችን የመሥራትና የመጠገን ጥረቶች ውስጥ  የኢንስቲትዩቶቹ ማኅበረሰብ በንቃት ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡

ድጋፉ የተደረገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ዩኒቨርሲቲው በዚህ አስከፊ ወቅት ከጎናቸው መሆኑን በተግባር ስላሳየ ያላቸውን ምስጋናና ክብር ገልፀዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት