በዩኒቨርሲቲው የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተላላፊና ተላላፊ ባልሆነ በተለምዶ ‹‹ዝሆኔ›› ተብሎ በሚጠራው በሽታ መከላከልና ሕክምና አሰጣጥ ዙሪያ ከደቡብ ክልል 20 ወረዳዎች ለተወጣጡ 200 የጤና ባለሙያዎች ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ ሥልጠናው ለ3 ቀናት የሚቆይና በ6 ዙር የሚሰጥ ነው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ዮሐንስ እንደገለጹት ሥልጠናው ማዕከሉ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው መሆኑን ጠቅሰው የሥልጠናው ተሳታፊዎችም በደቡብ ክልል በሽታው በስፋት ከሚታይባቸው 20 ወረዳዎች የተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ሥልጠናው በዋናነት በተለምዶ ‹‹ዝሆኔ›› ተብሎ በሚጠራው በሽታ ላይ ያተኮረ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ጤና ባለሙያዎች ዘንድ ያለውን የግንዛቤ እጥረትና መዘናጋትን በመቅረፍ በሽታውን የመከላከልና የማከም ሁኔታን ለማሻሻል የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

ማዕከሉ በተዘነጉ ቆላማ አካባቢ በሽታዎች ዙሪያ ሥልጠናዎችን ከመስጠቱ ባሻገር በበሽታዎቹ ዙሪያ የምርምር ሥራዎችን በማካሄድ እንደ ሀገር በሽታዎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሎም ለማጥፋት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የሚመለከተው አካል እንደ ግብአት እየተጠቀመባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማዕከሉ ተባባሪ ተመራማሪና ከአሠልጣኝ አቶ ዓለማየሁ በቀለ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓለም ጤና ድርጅት የተዘነጉ ወይም ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ተብለው የተለዩ  20 መሆናቸውን ገልጸው በእኛ ሀገር ካለቸው ስፋት አንፃር የተለዩት በሽታዎች 9 መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ በሽታዎች በብዛት  በኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በብዛት የሚያጠቁ መሆናቸውን የተናገሩት ተመራማሪው አሁን ላይ ለጤና ባለሙያዎች እየተሰጠ ያለው ሥልጠና ሁለቱን በሽታዎች በመከላከልና በማከም ሂደት ወስጥ የተፈጠረውን መዘናጋት ለማስቀረት የታለመ ነው ብለዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሲስተር ሳራ ዘካሪያስ እና አቶ አንበሳው ወልዴ በሰጡት አስተያየት ሁለቱም በሽታዎች በአካባቢያቸው የሚታዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን በሽታዎቹን ለመከላከልና ለማከም እምብዛም ጥረት እንደማይደረግ ጠቁመው በሥልጠናው በሽታዎቹን ከመከሰታቸው በፊት በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል እንዲሁም ከተከሰቱ በኋላ በቀላሉ ማከምና ማዳን እንደሚቻል ግንዛቤ አግኝተናል ብለዋል፡፡ ወደ ወረዳዎቻቸው ተመልሰው ያገኙትን ዕውቀትና ክሂሎት ወደ ተግባር በመቀየር የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ቃል ገብተዋል፡፡

ትራኮማ፣ ቢልሀርዚያ፣ ጊኒዎርም፣ እከክ፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትል እንዲሁም ተላላፊና  ተላላፊ ያልሆነ ዝሆኔ የተዘነጉ ወይም ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ከሚባሉት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት