የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት አባላትና አመራሮች በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች እየተከናወኑ የሚገኙ የግንባታ ሥራዎች ያሉበትን ሁኔታ ሐምሌ 10/2012 ዓ/ም ጎብኝተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን ጉብኝቱ በዩኒቨርሲቲ በካፒታል በጀት እየተገነቡ ያሉ የተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ያሉበትን የአፈፃፀም ደረጃና ተግዳሮቶች በአካል በማየት ለቀጣይ ሥራዎች አቅጣጫና ውሳኔ ለመስጠት የሚረዱ ሀሳቦች ለማግኘት የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ መሰል ጉብኝቶች ለዘርፉ ያላቸው ፋይዳ ጉልህ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ ታሪኳ በዩኒቨርሲቲው ተጀምረው የቆዩ በዋናው ግቢና ዓባያ ካምፓስ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ከኮንትራክተሮቹ ጋር የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን እንዲሁም ሌሎች ስትራቴጂዎች ተቀይሰው እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

በ2013 በጀት ዓመት ከሪፈራል ሆስፒታል የፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክት በስተቀር በመንግስት የተፈቀደ አዲስ ፕሮጀክት አለመኖሩን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቷ በበጀት ዓመቱ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ነባር ፐሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት አድርገን እንሠራለን ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ከ2001-2002 ዓ/ም ባሉት ዓመታት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ደካማ መሆኑን ጠቁመው ነገር ግን በ2010 ዓ/ም አካባቢ የተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም አበረታች ሲሆን ይህም የሆነው ከቀደሙ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተሞክሮ በመውሰድ ከዲዛይን ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ነው ብለዋል፡፡ አብዛኛዎቹ አዳዲስ ግንባታዎች በ2013 የትምህርት ዘመን ወደ ሥራ እንደሚገቡ የተናገሩት ዶ/ር ዳምጠው ሕንፃዎቹን ሥራ ለማስጀመርና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማሟላት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ከጉብኝቱ ተሳታፊ አመራሮች የአካዳሚክ ጉ/ም/ ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ የሚገኙ የግንባታ ሥራዎችን መስክ ላይ ሄደን ምልከታ ማድረጋችን የግንባታ ፕሮጀክቶቹ ያሉበትን አፈፃፀምና ችግሮቻቸውን በአግባቡ በመረዳት ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለመስጠት ይረዳል ብለዋል፡፡ በጉብኝቱ በተለይ በዩኒቨርሲቲው በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተጀመሩ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-መፃህፍት፣ ቤተ-ሙከራና ወርክሾፖችን ያካተቱ የግንባታ ፕሮጀክቶቹ እየተጠናቀቁ መሆናቸውን እንደታዘቡ የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ የግንባታ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡ የመማር ማስተማሩን ሥራ ከማሻሻል አኳያ ፋይዳቸው ጉልህ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የግንባታ ፕሮጀክቶች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቤዛ ተስፋዬ በበኩላቸው ጉብኝቱ በግንባታ ሥራ ሂደት ውስጥ ውሳኔ ሰጪ የሆኑት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች የግንባታ አፈፃፀሞችን በዝርዝር እንዲያውቁ መደረጉ ለሥራው ስኬት ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ካምፓሶች 28 ነባርና አዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ሲሆን ከበጀት አንፃርም ከ3 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ መሆናቸውን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት